Welcome
Login

Sport


 • አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተጫዋቾችን ጠርተዋል

   

  አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ተጫዋቾችን መርጠዋል፡፡

  አሰልጣኙ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጋና ከተሸነፈው ስብስብ መጠነኛ ለውጦች ያደረጉ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችም ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡

  የድሬዳዋ ከተማው ሳምሶን አሰፋ ጥሪ ሲቀርብለት ዋናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ከስብስቡ ውጪ ሆኗል፡፡

  በግራ ተከላካይ መስመር የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን እና የሀዋሳ ከተማው አምበል ደስታ ዮሀንስ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ 

  በአንጻሩ አዲስ ተስፋዬ እና ተስፋዬ በቀለ ከጋናው ቡድን ተቀናሽ ሆነዋል፡፡

  በአማካይ ስፍራ ሽመልስ በቀለ ለጨዋታው ተገቢ ባለመሆኑ እና ጋቶች ፓኖም በቅርቡ ወደ ሩሲያ በማቅናቱ በቡድኑ አልተካተቱም፡፡

  ብሩክ ቃልቦሬም ከስብስቡ ውጪ ሲሆን፥ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ በኃይሉ አሰፋ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ምንተስኖት አዳነ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለሞን በእነርሱ ምትክ ተጠርተዋል፡፡

  የንግድ ባንኩ ቢንያም በላይ ጥሪ ቢደረግለትም ለሙከራ ወደ ጀርመን በማቅናቱ በቡድኑ ሳይካተት ቀርቷል፡፡

  በአጥቂ መስመር ኡመድ ኡኩሪ ለጨዋታው ተገቢ ባለመሆኑ ሲቀነስ ተጨማሪ ተጫዋች ቡድኑን አልተቀላቀለም፡፡

  አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቻን 2018 ማጣሪያ ጅቡቲን የሚገጥመው ስብስባቸውን ይዘው ወደ ድሬዳዋ ያመራሉ፡፡

  ለማጣሪያው የመተመረጡ ተጫዋቾች፤

  ግብ ጠባቂዎች

  ጀማል ጣሰው (ጅማ አባ ቡና)፣ ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ) እና ለአለም ብርሃኑ (ሲዳማ ቡና)

  ተከላካዮች

  አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሳልሃዲን በርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱልከሪም መሃመድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፣ ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ)፣ ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት)፣ ደስታ ዮሀንስ (ሀዋሳ ከተማ) እና አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከነማ)

  አማካዮች

  ሽመክት ጉግሳ (ደደቢት)፣ ሙሉአለም መስፍን (ሲዳማ ቡና)፣ ጋዲሳ መብራቴ (ሃዋሳ ከተማ)፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) እንዲሁም ምንተስኖት አዳነ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

  አጥቂዎች

  ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አብዱልራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከነማ) እና ሳልሃዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ሆነው ተመርጠዋል፡፡

   

   

  Read more »
 • ዋልያዎቹ በባህር ዳር ለምን ደመቁ?

  ዋልያዎቹ  በባህር ዳር ለምን ደመቁ?

  በአዝመራው ሞሴ

  የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድን የመጀመሪያ  የአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን ማጣሪያ የነጥብ ጨዋታዎችን  አሸንፎ ሙሉ  ነጥብ በማግኘት አጀማምሩን አሳምሯል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በአህጉራዊ ውድድር ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎችን ከአዲስ አበባ ውጭ ሲያደርግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

  በጨዋታው ዋልያዎቹ የጨዋታ ብልጫ ወስደው  በተጋጣሚ መረብ ላይ  አራት ጎሎችን ሲያሰርፉ፣ አንድ ጎል ደግሞ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ ቡድኑ በተለይ በቻን ማጣሪያ በኬኒያ ላይ የወሰደው የበላይነት የብዙዎቹን ቀልብ የሳበ ሆኗል፡፡

  አሰልጣኙ በቅርብ ዋሊያዎቹን ከመሩት ሁለት የአሰልጣኝ ቡድኖች ውስጥ ቢያንስ ግማሽ ተጨዋቾችን ቀንሰው ውጤታማ መሆናቸው ደግሞ ደጋፊው ለአዲስ ተስፋ እንዲዘጋጅ ምክንያት ይሆናል፡፡

   

  የሜዳው እና ደጋፊው ሚና

  ብሔራዊ ቡድኑ  በግዙፍ የባህር ዳር ብሔራዊ  ስታዲዮም ከየትኛውም ጊዜ በበዛ ደጋፊ ፊት ታጅቦ መጫወት ለቡድኑም ሆነ ለስታዲዮሙ አዲስ ታሪክ ነው፡፡

  በስታዲዮም የታየው ደማቅ እና የማያቋርጥ የድጋፍም ለቡድኑ ድምቀት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡

  በሁለቱም ጨዋታዎች ደጋፊው በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ያሸበረቁ አልባሳትን በመልበስ፣ ቀለማትን በመቀባት እና የዋልያዎችን መለያ በመልበስ ስታዲዮሙን ሲንጥ ታይቷል፡፡

  በአዲስ አበባ ስታዲዮም ቡድኑ ሲመራ እና የጨዋታ ብልጫ በተጋጣሚው ሲወሰድበት የሚኖረው ዓይነት ፀጥታ በባህር ዳር ስታዲዮም አልነበረም፡፡

  የዚህ ማሳያ ዋሊያዎቹ በሌሴቶ 1ለ0 እየተመሩ ደጋፊው ይሰጥ የነበረው ያልተቋረጠ ድጋፍ ነው፡፡ በዚህም ዋሊያዎቹ ከእረፍት መልስ 2 ጎሎችን አስቆጥረው ጨዋታውን በድል እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡

  ይህም የተመልካቹ ድባብ ለቡድኑ ብርታት ሲሆን የተጋጣሚን ቡድን እንቅስቃሴ የሚረብሽ እንደነበር በግልጽ የታየበት ነው፡፡

  አስልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድናቸውን በባህር ዳር ይዘው ሲከትሙ የስታዲዮሙን ጥራት እንደ ዋና ምክንያት ቢወስዱም የደጋፊው ጫና ለተጋጣሚ ቡድኖች እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደሚሆን  አስቀድመው ያወቁ ይመስላል፡፡

  ሌላው ጉዳይ የባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲዮም የተመቸ የመጨወቻ ሜዳ መሆኑ ለተጨዋቾች እንክን የማይፈጥር ሆኗል፡፡ ለዚህ ይመስላል አንዳንድ የዋሊያዎቹ ተጨዋቾች በዚህ ሜዳ ኳስ በትክክል የማያቀብል ተጨዋች የማይችል ተጨዋች ነው በማለት የሜዳውን እንከን የለሽነት የገለጹት፡፡

  ሌሴቶ እና ኬኒያ ሲገመገሙ

  ሌሴቶ በአፍሪካ እግር ኳስ መድርክ ሊወሳ የሚችል ታሪክ የላትም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እሳቤም ዋሊያዎቹ በቀላሉ ሙሉ ነጥብ ለመውሰድ እንደማይቸገሩ አስገምቷል፡፡ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡

  በጨዋታው የሌሴቶ ቡድን ተከላክሎ ነጥብ ለመውሰድ የሚችል የተደራጀ ቡድን ሆኖ ታይቷል፡፡ ምንም ክፍተት ላለመፍጠር የነበራቸው ቅንጅትም ከኋላ ታሪካቸው ጋር ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ የዋሊያዎቹ አልፎ አልፎ የትኩረት ማጣት ለሌሴቶ የተመቸም ሆኗል፡፡

  ሌሴቶ በጨዋታው ማጠናቀቂያ በፈጠሩት አለመረጋጋት ለዋልያዎቹ እጃቸውን ሰጡ እንጅ ከባድ ቡድን መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ የቡድኑ ቅንጅት በመልሱ ጨዋታም ለዋሊያዎቹ ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡

  የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን በአንጻሩ ብዙ ተጠብቆ  ወርዶ የተጫወተ ቡድን ነው፡፡ አንድም አስደንጋጭ የግብ ሙከራ እና የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ያልቻለ ቡድን፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተቃራኒው የበለጠ የተቀናጀ እና ቶሎ ቶሎ ጫና መፍጠር የቻለበት ጨዋታ ነው፡፡

  የቡድኑ ተስፋዎች

  ከወራቶች በፊት ብሔራዊ ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ፈጥነው ውጤታማ መሆናቸው ከአሰልጣኙ ተስፋ ማድረግ የግድ እንድንል ያስችላል፡፡

  የመጀመሪያው እና ትልቁ ነጥብ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ቡድን መገንባት መቻላቸው ነው፡፡

  በተለይ በአሰልጣኝ ሰውነት እና ባሬቶ ዘመን የነበሩ የዋልያዎቹን ቁልፍ ተጨዋች ቀንሰው በአዳዲሶቹ ውጤታማ መሆን መቻላቸው መጭው ጊዜ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሩህ ሊሆን እንደሚችል እንደ አንድ ማሳያ መውሰድ ይቻላል ፡፡

  ለዓመታት በአንጋፋዎቹ ሲመራ የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ በወጣቶቹ ውጤታማ ሆኖ ማየት ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

  አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በተለይ በቻን ከሳላሃዲን በርጊቾ፣ስዩም ተስፋዬ፣ እና በሃይሉ አሰፋ ውጭ አዳዲስ ተጨዋቾችን ተጠቅመው ከውብ ጨዋታ ጋር ውጤታማ መሆን መቻላቸው ቡድኑ አዲስ መነቃቃት እየተፈጠረበት እንደሆነ ያሳያል፡፡

  ቡድኑ ኳስ በሚይዝበት ወቅት የሚታይበት መረጋጋትም የቡድኑን ብሩህ መንገድ የሚያሳይ ነው፡፡

  በጨዋታው በተከላካይ ክፍል ዘካርያስ ቱጂ፣ አስቻለው ታመነ፣ እንዲሁም ተካልኝ ደጀን  ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

  በተለይ የአስቻለው ታመነ እና የሳላሃዲን በርጊቾ ጥምረት ለዋሊያዎቹ የኋላ ደጅን አስተማማኝ መከታ መሆን እንደሚችል የታየበት ነው፡፡ ይህም በዋናነት በአይናለም እና ደጉ ደበበ ተንጠልጥሎ ለነበረው የብሔራዊ ቡድናችን የኋላ ደጀን ትልቅ ተስፋ ነው፡፡

  በመሃል ክፍል ጋቶች ፓኖም እና ፍሬው ስለሞን በባህር ዳር የነበራቸው ጊዜ መልካም የሚባል ነው፡፡

  አስቻለው ግርማ ፣ ራም ኬሎክ እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ የዋልያዎቹ የፊት መስመር ግርማ ሞገስ መሆን እንድሚችሉ በተለይ በቻን ጨዋታ  አሳይተዋል፡፡

  በግብ ጠባቂ በኩልም አቤል ማሞ እና ታሪክ ጌትነት የተሳካ  ጊዜን አሳልፈዋል፡፡

  እንደማደማደሚያ

  ቡድኑ በሁለቱም ጨዋታዎች ብዙ አውንታዊ ጎኖችን አሳይቷል፡፡ አሰልጣኙ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከዛምቢያው ጋር ካደረጉ ወዲህ  በቡድኑ ብዙ መሸሻሎችን አሳይተዋል፡፡

  ነገር ግን ይህ ቡድን  ከሜዳው ውጭ ገና አልተፈተነም፡፡ በሜዳውም እንደ አልጀሪያ ከመሰለ ቡድን ጋር ተጋጥሞ ነጥብ መያዝ የሚችል ቡድን ሊሆን ይግባል፡፡  

  ለዚህም በተለይ አዳዲስ ተጨዋቾችን በስነ ልቦናም ሆነ በቴክኒክ እና በታክቲክ ማደርጀት የአሰልጣኙ ሰፊ ስራ ነው 

   

   ebc.et 

   

  Read more »
RSS